መልዕክት

አቶ አለምአንተ አግደው ወንድሜነህ
የአብክመ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት እና የፍትሕና የሕግ ኢንስቲትዩት የቦርድ ሰብሳቢ
የአብክመ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት እና
የፍትሕና የሕግ ኢንስቲትዩት የቦርድ ሰብሳቢ መልዕክት
የዳኝነትና የፍትሕ አካላት የስልጠና ስርዓትት ለጠንካራ የዳኝነትና የፍትህ ስርዓት አንዱ ምሰሶ ነው። በሀገራችን ብሎም በክልላችን የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ሥልጠና ሥርዓት የመዘርጋት እና የተቋም ግንባታ ጉዳይ ረጅም የሚባል ጊዜን የቆየ ባይሆንም ሥርዓቱን በመቅረፅ እና ተቋም እንደገና በማደራጀት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የፍትህና የሕግ ኢንስቲትዩት በአዋጅ ቁጥር 299/2017 ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተጠሪ ሆኖ በክልላችን ለዳኞች፣ ለዐቃቤያነ-ሕግና ሌሎች የፍትሕ አካላት ስልጠና የሚሰጥ እንዲሁም የሕግ ጥናትና ምርመምር የሚያካሂድ የክልሉ የፍትሕና የሕግ የልህቀት ማዕከል ሆኖ ለማገልገል የተቋም ግንባታ የሪፎርም ሥራዎችን እየሰራ ሲሆን ይህን ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት ቀጣይነት ያላቸው የሪፎርም ሥራዎችን ማጠናከር ይጠበቅበታል፡፡ ኢንስቲትዩቱ ሥራውን በብቃት ማከናዎን እንዲያስችለውም የሕግ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገራት አቻ ተቋማት ጋር በአጋርነት የዳኝነት እና የፍትሕ ሥርዓትን ለማጠናከር ይሰራል፡፡

ደሴ ጥላሁን (ዶ/ር)
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የፍትህና የህግ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መልዕክት
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የፍትህና የሕግ ኢንስቲትዩት ተጠሪነቱ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሆኖ በክልሉ ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 299/2017 ዓ.ም እንደገና የተደራጀ የክልሉ መንግስት የፍትህና የህግ የልህቀት ማዕከል ነው፡፡ ኢንስቲትዩቱ የክልሉን የዳኝነትና የፍትህ አካላት ቀልጣፋ፤ ውጤታማ፤ ተደራሽ፤ ገለልተኛ እና የህዝብ አመኔታን ያረፉና እርካታን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ፤ የዳኝነትና የፍትህ ዘርፉን አመራሮችና ባለሙያዎች በዕውቀት፤ በክህሎት፤ እና በሥነ-ምግባር በማነፅ ዘርፉ ከፍተኛ ሙያዊ ብቃት እና ሥነ-ምግባር ባላቸው አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲገነባ በማስቻል፤ በጥናትና ምርምር ውጤት ላይ የተመሰረተ፤ የተተነተነ የፍትህ አስተዳደር ሥርዓት መረጃ ማዕከል በማበልፀግ፤ የዳኝነትና የፍትህ አካላት የሥልጠናና የጥናትና ምርምር የልህቀት ማዕከል ሆኖ የማገልገል ተልዕኮ ያለው ነው፡፡
ወቅታዊ ዜናዎች
የተቋሙ የትኩረት መስኮችና ተግባራት
ስትራቴጂያዊ የትኩረት መስክ
ተቋማዊ ፋሲሊቲና የመፈጸም አቅም ግንባታ |
የዳኝነት እና የፍትህ አካላት ሥልጠና |
የፍትህና የሕግ ጥናትና ምርምር |
ስእትራቴጂክ አጋርነት፤ ኮሚዩኒኬሽንና የገቢ አቅም ግንባታ |
የፍትሕና የሕግ መረጃ ማበልጸግና ዲጂታላይዜሽን |
ሥትራቴጂያዊ ውጤት
የተሻሻለ ተቋማዊ ፋሲሊቲና የተገነባ የመፈፀም አቅም |
በዕውቀት፤ በክህሎትና በሥነ-ምግባር የበቁ ዳኞች፤ ዐቃቤያነ-ህግና የፍትህ አካላት |
ችግር ፈቺ የፍትህና የህግ ጥናትና ምርምር ምክረ-ሃሳቦች |
የተፈጠረ አጋርነት፤ የተገነባ ገፅታና ያደገ ገቢ |
በዲጂታላይዜሽን የታገዘና የበለፀገ የፍትህና የሕግ መረጃ |
የዋና ዳይሬክተሩ ሥልጣን እና ተግባራት
፩/ ዋና ዳይሬክተሩ የኢንስቲትዩቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን የኢንስቲትዩቱን ሥራዎች ይመራል፣ ያስተዳድራል፡፡
፪/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) ላይ የተመለከተው አጠቃላይ አነጋገር እንደተጠበቀ ሆኖ፡
ሀ) በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፮ ላይ የተመለከተዉን የኢንስቲትዩቱን ሥልጣን እና ተግባራት ሥራ ላይ ያውላል፤
ለ) ዕቅድ እና መርሐ-ግብር አዘጋጅቶ ለቦርዱ ያቀርባል፣ ሲፈቀድም በሥራ ላይ ያውላል፤ በቦርዱ በኩል ታይቶ ለክልሉ ገንዘብ ቢሮ በማቅረብ የጸደቀለትን የኢንስቲትዩቱን በጀት ስራ ላይ ያውላል፤
ሐ) የሥልጠና ካሪኩለም፣ የምርምር መርሐ-ግብሮችን እና የመፍትሔ ወይም ውሳኔ ሀሳቦችን ለቦርድ አቅርቦ ያስፀድቃል፤
መ) ለኢንስቲትዩቱ በተፈቀደው በጀት እና የሥራ መርሐ-ግብር መሰረት ገንዘብ ወጪ ያደርጋል፤
ሠ) የኢንስቲትዩቱን ባለሙያዎች እና የአስተዳደር ሰራተኞች ይቀጥራል፤ ያስተዳድራል፤
ረ) ከሦስተኛ ወገኖች ጋር በሚደረጉ ግንኙነቶች ሁሉ ኢንስቲትዩቱን ይወክላል፤
ሰ) የኢንስቲትዩቱን የሥራ አፈጻጸም እና የሂሳብ ሪፖርት አዘጋጅቶ ለቦርዱ ያቀርባል፤
ሸ) ከቦርዱ የሚሰጡትን ሌሎች ተዛማጅ ተግባራት ያከናውናል፡፡
፫/ ዋና ዳይሬክተሩ ለኢንስቲትዩቱ ሥራ ቅልጥፍና በሚያስፈልግ መጠን ከሥልጣን እና ተግባራቱ በከፊል ለምክትል ዋና ዳይሬክተሮች እና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች በውክልና ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡
የምክትል ዋና ዳይሬክተር ሥልጣን እና ተግባራት
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር፡-
፩/ በኢንስቲትዩቱ ድርጅታዊ መዋቅር መሠረት የሚመለከተዉን የሥራ ዘርፍ ይመራል፤ ያስተዳድራል፤
፪/ በዋና ዳይሬክተሩ ተለይተው የሚሰጡትን ተግባራት ያከናውናል፤
፫/ ተለይቶ ካልተወከለ በስተቀር ዋና ዳይሬክተሩ በማይኖርበት ጊዜ በሹመት ቅድሚያ ያለው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተክቶት ይሠራል፡፡
፲፫. በጀት
የኢንስቲትዩቱ የበጀት ምንጮች የሚከተሉት ይሆናሉ፤
፩/ በክልሉ መንግስት የሚመደብ በጀት፤
፪/ ከሚሰበስበው የውስጥ ገቢ፤
፫/ ከሌሎች ምንጮች የተገኙ የገንዘብ ወይም የአይነት ድጋፎች፡፡
፲፬. የሂሳብ መዛግብት
፩/ ኢንስቲትዩቱ የተሟላና ትክክለኛ የሂሳብ መዛግብት ይይዛል፡፡
፪/ የኢንስቲትዩቱ የሂሳብ መዛግብት እና ገንዘብ ነክ ሰነዶች በክልሉ ዋና ኦዲተር ወይም በክልሉ ዋና ኦዲተር በሚሰየም ኦዲተር በየዓመቱ ይመረመራሉ፡፡
